ደቡብ ሱዳን ከከባድ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ግፊት በኋላ፣ አገሪቱ ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ለማካሄድ ቀን መቁረጧን አስታወቀች።
ነገር ግን ቀድሞ የአገሪቱ የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩትና በአሁኑ ወቅት በትግል ላይ በሚገኙት ዶ/ር ሬክ ማቻር የሚመራው ትልቁ ተቃዋሚ ቡድን ይህንን ውሳኔ ተቃውሟል። ተቃዋሚው ወገን በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት እና በእነሱ መካከል ያሉ መሠረታዊ የፖለቲካና የጸጥታ ችግሮች ሳይፈቱ የምርጫ ቀን መቁረጥ አደገኛ አካሄድ ነው ሲል ስጋቱን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት "የአገር ክህደት" ክስ ተመስርቶባቸው አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት ሬክ ማቻር፣ በምርጫው ላይ በነጻነት ለመወዳደር ከእስር እንደሚፈቱ ወይም እንደማይፈቱ መንግስት እስካሁን በግልጽ ያለው ነገር የለም።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራባውያን አጋሮች፣ ዋናው የተቃዋሚ መሪ ሬክ ማቻር በእስር ላይ እያሉ በአገሪቱ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊ ሂደትና ምርጫ ተቀባይነት የለውም የሚል አቋማቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ካገኘች ማግስት ጀምሮ በገጠማት የእርስ በርስ ጦርነትና አለመረጋጋት ምክንያት እስካሁን አጠቃላይ ምርጫ አድርጋ አታውቅም።