በመካከለኛው ምስራቅ ለረጅም ጊዜ ሲያገረሽ የቆየውን ውጥረት ለማርገብና ዓለም አቀፉን የኃይል አቅርቦት መስመር ሰላማዊ ለማድረግ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በቅርቡ የተደረሰው ታሪካዊ የተኩስ አቁም እና የጋራ መግባቢያ ስምምነት (MoU) ፈተና ውስጥ መውደቁ ተሰማ።
የኢራን ማዕከላዊ ወታደራዊ ዕዝ እንደገለጸው፤ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሂዝቦላህ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት የመጀመሪያ እና መሠረታዊ አንቀጽ የሚጥስ በመሆኑ፣ ስትራቴጂካዊውን የሆርሙዝ ሰርጥን በድጋሚ ሙሉ በሙሉ መዝጋቱን በይፋ አስታውቋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ባሕር ኃይል ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፥ ይህ እጅግ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ለሁሉም ዓይነት የንግድና የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ዝግ መሆኑን አስታውቋል። ማንኛቸውም መርከቦች ወደ ሰርጡ የሚቃረቡ ከሆነ ለከፍተኛ አደጋ እና ለወታደራዊ ጥቃት ስለሚጋለጡ፣ መርከቦቻቸውን ከሆርሙዝ ሰርጥ በአስቸኳይ እንዲያርቁና አቅጣጫ እንዲቀይሩ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ይህ ውሳኔ የተሰማው ሁለቱ አገራት የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ፣ ባለፉት ቀናት በተለይም ዓርብ ዕለት የባሕር መተላለፊያው ሙሉ ለሙሉ ክፍት ሆኖ መርከቦች ማለፍ ከጀመሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሆኑ ቀውሱን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
አብዮታዊ ዘቡ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ባቀረበው ይፋዊ መግለጫ፥ ስምምነቱ በአሜሪካና በእስራኤል በኩል ባለመከበሩ ሰርጡ ተመልሶ እንዲዘጋ መገደዱንና ይህም ለተፈጠረው የስምምነት መፍረስ እንደ መጀመሪያ እርምጃ የሚቆጠር መሆኑን ገልጿል።
ኢራን ከአሜሪካ ጋር በደረሰችው የ60 ቀናት ጊዜያዊ የመግባቢያ ስምምነት ላይ፥ በሊባኖስና በሌሎችም ግንባሮች ላይ የሚካሄዱ ወታደራዊ ጥቃቶች በአስቸኳይ እና በቋሚነት እንዲቆሙ የሚል ግልጽ ቃል መካተቱን ጠቅሳለች። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም የእስራኤል መከላከያ ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ የሚያደርገውን የአየርና የምድር ጥቃት ባለማቆሙ፣ ዋሺንግተን እስራኤልን የመግታትና የገባችውን ቃል የመጠበቅ ግዴታዋን አልተወጣችም ስትል ቴህራን ወቅሳለች።
የቢቢሲ እና የአልጀዚራ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፥ ኢራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው አሜሪካ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ረገድ የገባችውን ቃል እንድታከብር ግፊት ለማድረግ ነው።
በሌላ በኩል፥ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ እና የማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) የኢራንን መግለጫ ያስተባበሉ ሲሆን፥ የሆርሙዝ ሰርጥ በኢራን ቁጥጥር ስር እንዳልሆነና የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ አሁንም በአሜሪካ የባሕር ኃይል ጥበቃ ሥር እየቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ፍጥጫ በስዊዘርላንድ ሊጀመር በታቀደው የሁለቱ አገራት የኒውክሌርና የሰላም ውይይት ላይ ትልቅ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዓለም የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት አንድ አምስተኛ የሚሻገርበት ይህ ስትራቴጂካዊ የውኃ መስመር መዘጋቱ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የኃይል ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረትና ቀውስ እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት ገብቶታል።