አምዶች

Logo ከይር ታይምስ

የዲጂታል ዜና እምብርት

የቅርብ ዜና
የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ሐውልት ምረቃ፤ ከኪነ-ጥበብ ክብር ባሻገር ያለው የሥራ ዕድልና የቱሪዝም ፋይዳ የዜጎች ክብር የዲፕሎማሲያችን ኹሉ ቊንጮ ይኹን!  ያገለገሉ መኪኖች; ቁርጥራጭ ብረቶች ጨረታ የጣና ሆቴል ዳግም ልደት : ከ3.3 ቢሊዮን ብር በስተጀርባ ያለው ግዙፍ እቅድና ተግዳሮ በ98 ቢሊዮን ብር ዘረፋ የተሳተፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ታዋቂ አርቲስቶች በኦዲት ተጋለጡ የሆርሙዝ ወሽመጥ እጣ ፈንታና የኢራን አዲሱ የሰላም እቅድ «ልመና በቃን፤ ወደ ቀድሞ ቀያችን ተመልሰን ራሳችንን መርዳት እንፈልጋለን» - ተፈናቃዮች የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ሐውልት ምረቃ፤ ከኪነ-ጥበብ ክብር ባሻገር ያለው የሥራ ዕድልና የቱሪዝም ፋይዳ የዜጎች ክብር የዲፕሎማሲያችን ኹሉ ቊንጮ ይኹን!  ያገለገሉ መኪኖች; ቁርጥራጭ ብረቶች ጨረታ የጣና ሆቴል ዳግም ልደት : ከ3.3 ቢሊዮን ብር በስተጀርባ ያለው ግዙፍ እቅድና ተግዳሮ በ98 ቢሊዮን ብር ዘረፋ የተሳተፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ታዋቂ አርቲስቶች በኦዲት ተጋለጡ የሆርሙዝ ወሽመጥ እጣ ፈንታና የኢራን አዲሱ የሰላም እቅድ «ልመና በቃን፤ ወደ ቀድሞ ቀያችን ተመልሰን ራሳችንን መርዳት እንፈልጋለን» - ተፈናቃዮች
ፖለቲካ / የፖለቲካ ፓርቲዎች እ.ኤ.አ.: May 5, 2026

የዜጎች ክብር የዲፕሎማሲያችን ኹሉ ቊንጮ ይኹን! 

News Image

ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ለሰቆቃ ስለተጋለጡ ዜጎች የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያዊያን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ያለ ቪዛ ወደ ውጪ አገር ለትምህርት በሚላኩበት ወቅት ፈተናቸውን አልፈው የምረቃ ሥነሥርዓት እንኳን ሳይጠብቁ ተሳፍረው ወደ አገራቸው ይመለሱ ነበር። ኢትዮጵያ ከምእራቡ ዓለም ጋር ሲነጻጸርም ደካማ የኢኮኖሚ ደረጃና የማኅበራዊ ግልጋሎትም አልነበራትም። የምእራቡ ዓለም ምቾት የአገር ፍቅርንና የእናት ቤት ሽሮን የሚያስንቅ አልነበረም። አንድ ሰው ከተማረ ተከብሮ አገሩ ያገለግላል። ማኅበረሰቡም ይኮራበት ነበር።

ይኹንና በመጨረሻው ያለንን ኹሉ አፍርሰን እንደ ቻይናና ሦቪዬት ኅብረት ሦሻሊዝምን፣ የስታሊንን የብሔር ብሔረሰቦች ፓለቲካ ብንተክል የተሻለ እንኾናለን ተባለ። ያም ኢትዮጵያን ወደ ምድራዊ ሲዖል ቀየረ። ስደት እንደ ጌጥና ልዩ እድል ተቆጠረ። አዛውንቶችንና አርበኞችን በጅምላ መረሸን፣ ወጣቱን በቀይ ሽብር መጨረስ እድል ፈንታችን ኾነ። በዚያም ሳይበቃ ቀጥሎ የመጣው ደግሞ መጤ፣ ነፍጠኛ፣ ኦርቶዶክስ፣ ሴማቲክስ እያለ ምድሪቷን በደም አጠባት። ምንም የማያውቁ ሕጻናት ለሰቆቃ የሚዳረጉበት፣ እርጉዝ እናት በአሰቃቂ የምትገደልበት ዘመን መጣ፣ አለ፣ ደርሰን ካላስቆመነው ይቀጥላል።

ይኽን ግፍና አድሏዊነት ፈርቶ የሚሸሸው ከመጥበሻው ወደ እሳቱ፣ ጅብ ፈርቸ ዛፍ ብወጣ ነብር ቆዬኝ እየኾነ መጣ። እስከአኹን በወጣ ይፋዊ መረጃ በዚኽ ሣምንት ብቻ ከ7 በላይ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን Xenophobia(መጤ ጥላቻ) በተሰኘ ዘመናዊ አፓርታይድ አስተሳሰብ ወንድሞቻችን በአሰቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል። ትናንት ለአፍሪካውያን ከባርነትና ና ነጻነት በተለይ ለደቡብ አፍሪካውያን የበዛ ግፍ አገዛዝ ለማላቀቅ እነኔልሰን ማንዴላን ዜግነት ሰጥታ፣ ወታደራዊ ስልጠና፣ ስንቅና ትጥቅ ቋጥራ ለነጻነት ጎሕ የቀደደች አገር ዜጎች ለውለታቸው መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸው በድባብና ቀይ ምንጣፍ መሄድ ሲገባቸው በጉልበታቸው ጥረው ግረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን መሳደድና መገደል እጅጉን አስቆጥቶናል፤ ለፀፀት ዳርጎናል። ትብብራችን በግፍና በደቦ ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ልባዊ ሐዘኑን ይገልጻል። 

በሌላ በኩል በሳውዲ አረቢያ ምድር በአገሬው ሕግ(ሸሪዓ) መሠረት ከ 60 በላይ ኢትዮጵያውያን የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ እንዳለ ዓለም አቀፍ ተቋማት ካወጡት ሪፖርት መረዳት ችለናል። ይኽም እንደዜጋና የሕዝብ ሕመም እንደሚሰማው ፓርቲ ልባችን ክፉኛ ተነክቷል። በእርግጥ ይሄ ስደተኞችን ምክንያት እየፈለጉ ማጥቃት በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣ አባዜ አካል ነው ብለን እናስባለን። ኢትዮጵያና ሳውድ አረቢያ ከንግድና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዘለለ የቀደመ የሚባል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትስስር ያላቸው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በሃይማኖት፣ በምግባር አገሩን ያቀኑበት ትስስሩን ያጎለበቱበት ይልቁኑም ኢትዮጵያ የነቢዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች የኾኑ ካዕባዎችን በአገራቸው በዕምነታቸው ምክንያት ተሳደው ሲመጡ ለዘር አትርፎ ያቆዬ ሕዝብና አገር ነው። በዚኽም ኢትዮጵያ እስልምናን ከመጥፋት የታደገች ግምጃ ቤት ናት ቢባል ማጋነን አይኾንም።

የዚኹ ውለታዋና ክብሯ እንደተጠበቀ ኾኖ የትኛውም ሰው በየትም ቦታ በወንጀል ከተገኘ በፍትሕ አደባባይ መቅረቡን በጽኑ የምናምነውና የምንከራከርለት መርሕ ቢኾንም እነዚኽ ኢትዮጵያውያን ላይ የመጨረሻው የጭካኔ ፍርድ መፈጸሙን በጽኑ እንቃወማለን። ነገሩ በቅርብ ጊዜያት ወዲኽ እያቆጠቀጠ የመጣውን ስደተኛ ጠልነት ጋር የተገናኘ እንጂ በወንጀል  እንዳልኾነ ጥርጣሬው አለን። ይኽም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አድርገን እንደምንቆጥረው የሳውዲ መንግሥትና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቅልን እንሻለን። 

ስለኾነም፣
1. የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በኢትዮጵያውያንና በመላው አፍሪካውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የግፍ ግድያና ማሳደድ እንዲያስቆም ለሞቱትም አግባብ ያለውን ማቋቋሚያና ካሳ እንዲሰጥ አፍሪካ ሕብረትና ዓለምአቀፍ ተቋማት ጫና እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። 

2. የኢትዮጵያ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደውን የግፍ ግድያ ማስቆም የድፕሎማሲ ሥራው ኹሉ ቊንጮ መኾኑን መረዳት አለበት ብለን እናምናለን። ውቂያኖስ አቋርጦ ስለሌሎች አገር ዜጎች መገደል ጥብቅና ሲቆም ያየነው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ይሄንን በጉያው የሚፈጸም የግፍ ግድያ ማስቆም ካልቻለ በአፍሪካ ኅብረት ያለውን ተሳትፎ ጭምር እንዲጤን ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በመኾን ግፊት እንዲደረግ ጥሪ እናቀርባለን።

3. ኢትዮጵያ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነትና የኢትዮጵያን ውለታ በማውሳት መንግሥት በመታረጃው ቄራ ቆመው የሞት አፋፍ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን እንዲታደግና ጣልቃ ገብቶ የሞት ፍርዱ ወደ እሥራት እንዲቀየር ብሎም በአገራቸው እንዲዳኙ አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ኹሉ እንዲያደርግ እናሳስባለን። 

4. መንግሥት የችግሩ መነሻ የኾነውን፣ በአገር ውስጥ መኖር የማያስችሉና ለስደት የሚዳርጉ አገራዊ ቀውሶችን እንዲያስቆም እናሳስባለን። 

ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት - ለኢትዮጵያ
ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
***

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ