| ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 76ኛው ዙር የመመረቂያ በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር | ከይር ታይምስ
አምዶች
የቅርብ ዜና
ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 76ኛው ዙር የመመረቂያ በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አዲሱ የትምህርት ሪፎርም የሀገሪቱን መዋቅራዊ ስብራት ለመጠገን ወሳኝ መሆኑን ገለጹ አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ የኢራንን ይዞታዎች አጋየች! የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለቀጣዩ ሀገራዊ ውይይት መነሻ የሚሆኑ ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ አደረገ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታወቁ በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ማሸነፉ ተገለጠ ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፍ ግፊት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ ልታካሂድ ቀጠሮ ቆረጠች ግዙፉ የፈረንሳይ የነዳጅ ኩባንያ ቶታል ኢነርጂ ከ75 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ነው ባይናንስ በኢትዮጵያ ውስጥ አቋርጦት የነበረውን የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት አገልግሎት በድጋሚ ጀመረ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክርስቲያን ታደለ እና ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ላይ ሊሰጥ የነበረውን ብይን አዛወረ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 76ኛው ዙር የመመረቂያ በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አዲሱ የትምህርት ሪፎርም የሀገሪቱን መዋቅራዊ ስብራት ለመጠገን ወሳኝ መሆኑን ገለጹ አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ የኢራንን ይዞታዎች አጋየች! የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለቀጣዩ ሀገራዊ ውይይት መነሻ የሚሆኑ ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ አደረገ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ አስታወቁ በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ማሸነፉ ተገለጠ ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፍ ግፊት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ ልታካሂድ ቀጠሮ ቆረጠች ግዙፉ የፈረንሳይ የነዳጅ ኩባንያ ቶታል ኢነርጂ ከ75 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ነው ባይናንስ በኢትዮጵያ ውስጥ አቋርጦት የነበረውን የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት አገልግሎት በድጋሚ ጀመረ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክርስቲያን ታደለ እና ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ላይ ሊሰጥ የነበረውን ብይን አዛወረ
ነፃ ሃሳብ / ይፋዊ ንግግሮች

ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 76ኛው ዙር የመመረቂያ በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር

በያፌት ግርማ | June 27, 2026

ክቡራትና ክቡራን፤

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤ በተለይም ደግሞ የዕለቱ የክብር ባለቤቶች—ውድ የዚህ ዙር ተመራቂዎች፤ እንኳን ለዚህ ታላቅ ማዕረግና የደስታ ቀን በሰላም አደረሳችሁ!

ዛሬ በዚህ ታሪካዊ አዳራሽ ውስጥ የሚታየው ደስታና በፊታችሁ ላይ የሚበራው ተስፋ፣ የእናንተ የአመታት ድካምና የጽናት ውጤት ብቻ አይደለም። አዲሱ የትምህርት ሪፎርማችን ከተጀመረ በኋላ ያስመረቅናችሁ የመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች እንደመሆናችሁ፣ ይህ ቀን በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት ታላቅ ዕለት ጭምር ነው። ለዚህም ነው ከእናንተ በተጨማሪ ይህ ቀን እውን እንዲሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ—ድካማችሁ ፍሬ አፍርቷልና እንኳን ደስ አላችሁ የምለው። ዛሬ ለሀገራችሁና ለህዝባችሁ እድገት የበኩላችሁን የምታበረክቱበትን በቂ እውቀት ታጥቃችሁ እንደወጣችሁ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

ውድ ተመራቂዎች፤ በአለም ታሪክ ዝቅተኛ ከሚባል የኢኮኖሚ ደረጃና የድህነት አረንቋ ወጥተው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የላቀ የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉ ሀገራትን ተሞክሮና የሪፎርም ጉዞ በአግባቡ መረዳት ለሀገር ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ካደረግነው የትምህርት ተሃድሶ ጋር ተቀራራቢ የሚመስል እርምጃ ከወሰዱ ሀገራት መካከል ቻይናን ብንወስድ፣ አሁን ለደረሰችበት የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ልዕልና መሰረት ከሆኗት የለውጥ እርምጃዎች ቀዳሚው በትምህርት ዘርፍ ላይ የወሰደችው ቁርጠኛ የሪፎርም እርምጃ ነው። በ1970ዎቹ አጋማሽ፣ "ታላቁ የልማት እርምጃ" (Great Leap Forward) እና "የባህል አብዮት" (Cultural Revolution) ያሉ ክስተቶች በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ላይ ከፍተኛ ምስቅልቅል ፈጥረው ነበር። በወቅቱ ዩኒቨርሲቲዎችን "የፀረ-አብዮት መናፈሻ" አድርጎ በመፈረጅ ከፍተኛ የትምህርት መስተጓጎል ተፈጥሮ እንደነበር ከታሪካቸው ማየት ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ የታሪክ ጠባሳ ለመውጣት የቻይና የለውጥ አራማጆች የወሰዱት ቀዳሚ እርምጃ ተቋርጦ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና እንደገና በተጠናከረ መንገድ ማስጀመርና ተቋማቱን ነጻ፣ ገለልተኛ የእውቀት ማዕከላት ማድረግ ነበር። ዛሬ ሀገሪቱን የአለም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረጋት ይህ ከታች የተጀመረው ልዩ ትኩረት ነው።

ከከፋ ድህነት ተነስታ በትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት ላይ በመስራት የአለም የቴክኖሎጂ ሃያል መሆን የቻለችው ሌላኛዋ ሀገር ደቡብ ኮሪያ ናት። በ1950ዎቹ ከኮሪያ ጦርነት ማብቂያ በኋላ ሀገሪቱ ምንም አይነት የተፈጥሮ ሃብት ያልነበራትና በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የምትገኝ ነበረች። የኮሪያ መንግስት ሀገሩን ለመለወጥ ብቸኛውና ዋነኛው ሀብት **"የሰው አእምሮ"** መሆኑን በመገንዘብ፣ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ባጀት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ወደ ትምህርት ዘርፍ አዞረ። መጀመሪያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ዜጋ እኩል፣ ነጻና ግዴታ በማድረግ የፊደል መቁጠር ምጣኔን (Literacy Rate) በአጭር ጊዜ ውስጥ 100% አደረሱ። በመቀጠልም መካከለኛና ከፍተኛ ትምህርትን ከኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ፍላጎት ጋር በማጣጣም፣ ዛሬ እንደ ሳምሰንግ ያሉ የአለም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ባለቤትና በፈጠራ ስራ ከአለም ግንባር ቀደም መሆን ችለዋል።

ከነዚህ ሀገራት የምንማረው ታላቅ እውነት ቢኖር፣ አንድን ሀገር ከድህነት አረንቋ አውጥቶ ወደ እድገት ማማ መውሰድ የሚቻለው በተፈጥሮ ሃብት መብዛት ሳይሆን፣ እንደ ሀገር ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የትምህርት ስርአት መገንባት ሲቻል ብቻ መሆኑን ነው።

እኛም እንደ ሀገር ከትናንት ታሪካችን ተምረን፣ የዛሬውን ተጨባጭ እውነት ተረድተን ለነገው መፍትሄ እንድንሆን እውነታውን ፊት ለፊት መጋፈጥ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ በተለይ ከደርግ መንግስት መምጣት ጀምሮ በትምህርት ስርአቱ ላይ የገጠሙትን መዋቅራዊ ችግሮች በግልፅ መረዳትና ማስተካከል ይኖርባታል።

ባለፉት አምስት አስርት አመታት ገደማ የነበሩ የፖለቲካ ስርአቶች፣ ትምህርትን በሰፊው ለማድረስ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፣ በትይዩ ግን ትምህርት ቤቶችንና የትምህርት ስርአቱን የርዕዮተ-አለም መቅረጫና የፖለቲካ ቁጥጥር ማዕከል ለማድረግ ሞክረዋል። ይህ ስር የሰደደ መዋቅራዊ ችግር በዋናነት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ መሆን የሚጠይቀውን "በነጻነት ማሰብ" ተነጥቀው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።

በሌላ በኩል፣ የአንድ ሀገር ትምህርት መሰረት የሚጣለው በቅድመ-ልጅነት (Early Childhood Education) ትምህርት ላይ ሆኖ ሳለ፣ ይህ ዘርፍ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ሳይሆን ቀርቷል። የተሻለ ግብአት ባላቸው የግል ትምህርት ቤቶችና መሰረታዊ አቅርቦት በሌላቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች መካከል የተፈጠረው ሰፊ ልዩነት፣ በዜጎች መካከል ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር እኩልነትን (ልዩነትን) ፈጥሮ ቆይቷል።

ጥራት የሌለው ትምህርት መዘዙ በክፍል ውስጥ ብቻ የሚቀር አይደለም። ዛሬ በአይናችን የምናየው እጅግ አደገኛ የታሪክ ጠባሳ፣ የማህበረሰብ መከፋፈልና የተቋማት መዳከም ዋነኛው መንስኤ የዚሁ የትምህርት ጥራት መውረድ ውጤት ነው። አንድን ትውልድ በእውቀትና በስነ-ምግባር ሳይቀረጹ ማውጣት፣ ለሀገር የሚተርፍ መዋቅራዊ ቀውስ እንደማዘጋጀት ይቆጠራል። በዚህም ምክንያት በሀገራችን ዛሬ የሀገሪቱ ታላቅ ሀብትና ሞተር መሆን የነበረበት የሰው ሃይል በእውቀት፣ በፈጠራና በክህሎት ሳይታነጽ ቀርቶ፣ የትውልዱ የሞራልና የግብረ-ገብነት መሰረት በመናጋቱ የጋራ አብሮነት ጠፍቶ "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" የሚል አደገኛ ግለኝነት ተስፋፍቷል።

ይህ የሞራል ቀውስ በቀጥታ ወደ መንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋማትም ዘልቆ በመግባት፣ ተቋማቱ ህዝብን በቅንነት፣ በታማኝነትና በፍትሃዊነት የሚያገለግሉ የዜጎች መታመኛ መሆናቸው ቀርቶ፣ ሙስናና አድሏዊ አሰራር የሰፈነባቸው እንዲሆኑና ሰፊውን ማህበረሰብ የሚያንገላቱ፣ የሰው ልጅ ክብርን የሚያዋርዱ የሞራል ውድቀቶች እንዲሰፍኑ አድርጓል።

ሀገራችንን አሁን ካለችበት ችግር ለማላቀቅና ወደ ላቀ የስልጣኔ ማማ ለማድረስ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የታነጹ፣ ለእውቀት ክብር ያላቸው ከፍተኛ የሰው ሃይል አቅም መገንባት ይኖርብናል። ዜጎች እኔ ብቻ ልኑር ከሚል ፍጹም ግለኝነት ወጥተው ስለሀገራቸው ክብርና እድገት የሚያስቡ፣ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በታማኝነት የሚወጡ መሆን ይኖርባቸዋል።

እንዲህ አይነት ዘርፈ ብዙ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ሴክተር የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት ተጀምረዋል። የወደፊት የኛ እውነተኛ ስኬት የሚረጋገጠው አዳዲስ እውቀቶችን በራሳችን ምድር ላይ ማፍራት ስንችል፣ እውቀትን ከስነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት ጋር አዋህደን ማስተማር ስንችልና የትምህርት ስርአታችንን ሙሉ በሙሉ የህዝባችንን ጥቅም ማእከል ያደረገ ማድረግ ስንችል ብቻ ነው።

 ችግሩን ከመሰረቱ የሚፈታ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አውጥተናል። በአዲሱ ስርአተ-ትምህርት መሰረት፣ ትምህርቱ በብቃት ላይ የተመሰረተ፣ ሀገር በቀል እውቀትን፣ የሙያና የቀለም ትምህርትን እንዲሁም የግብረ-ገብ ትምህርትን ያካተተ ሆኖ ተቀርጿል። ትምህርትን ከምርትና ከተግባር ጋር በማገናኘት፣ ትውልዱ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን የላቀ እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በቀደሙት ስርአቶች በከተሞች ብቻ የተገደበውንና በሀብታምና በድሃ ልጆች መካከል ሰፊ የዕድል ልዩነት የፈጠረውን መዋቅራዊ እኩልነት ለመስበር፣ ሰፊ ሀገራዊ ስራ ተከናውኗል። ከ30 በላይ አዳዲስ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ከአራት ሚሊዮን በላይ ህጻናት እኩልና ነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም ምንም አይነት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት በሌላቸው ወረዳዎች ላይ 1,452 ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን ይህ አመት ከማለቁ በፊት ለመገንባት ታቅዶ ስራው በከፍተኛ ፍጥነት በመካሄድ ላይ ነው።

 የመሰረተ ልማት ደረጃዎችን ማሻሻል፦ በአገሪቱ በተደረገው የኢንስፔክሽን ጥናት ከአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እስከ 86 በመቶ፣ እንዲሁም ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለመማር ማስተማር ሂደት የሚያስፈልጋቸው መሰረታዊ ግብአቶችና መሰረተ ልማት የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጧል። ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ይዞ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ስለማይቻል፣ ከዚህ በኋላ ለሚገነቡ ትምህርት ቤቶች አዲስ ስታንዳርድ በማውጣት በቂ መማሪያ ክፍሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የተግባር ልምምድ ቦታዎችና የእርሻ ማሳዎች ያላቸው ዘመናዊ ተቋማት እንዲገነቡ አዲስ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር እንዲዘጋጅ ተደርጓል።

 "የትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ፦ይህንን በነባር ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ችግር በመንግስት አቅም ብቻ መፍታት ስለማይቻል፣ በተጀመረው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡ በጉልበት፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ባደረገው ታሪካዊ ተሳትፎ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ታላቅ ስራ ተከናውኗል። ህብረተሰቡ ትምህርትን ለመደገፍ ወደ ኋላ እንደማይል በሚገባ አረጋግጠናል።

 የፌደራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች፦ የሀገራችን የወደፊት መሪዎች የሚሆኑ ችግር ፈቺና የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ለማፍራት፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በውጤታቸው የተመረጡ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች የሚማሩበት የፌደራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ይገኛሉ።

 የፈተና ምዘናና የአስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ፦ በሪፎርማችን ውስጥ ሌላው ልዩ ትኩረት የተሰጠው እናንተ ራሳችሁ በሂደት ያለፋችሁበት የፈተና ምዘና የአስተዳደር ስርዓቱን የማስተካከል ሂደት ነው። ባለፉት አመታት ኩረጃ፣ መረጃና ስርቆት ባህል ሆኖ፣ ስነ-ምግባር የጠፋበትና የተማሪዎች የማጥናት ፍላጎት በእጅጉ የወረደበት ስርዓት ሰፍኖ ቆይቷል። ይህንን ከመሰረቱ ለማስተካከል ባለፉት አራት አመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ በማድረግና የወረቀትና የኦንላይን ድብልቅ የፈተና ስርዓት በመዘርጋት ኩረጃንና ስርቆትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። በኩረጃና በስርቆት የሚገኝ ነገር እንደሌለ፣ በማጥናትና በልፋት ብቻ ውጤት እንደሚገኝ በሁሉም ዘንድ መተማመን እየፈጠርን መጥተናል። እናንተ የዚህ አመት ተመራቂዎች የዚህ እውነተኛ ውጤቶች ናችሁ።

የመምህራንን የማስተማር ብቃት ለማሳደግ በክረምት ወቅት ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንና ለትምህርት ቤት አመራሮች በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት ይዘትና ማስተማሪያ ስነ-ዘዴ ላይ ያተኮረ ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። በተመሳሳይ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክና አስተዳደራዊ ነጻነት እንዲኖራቸው እየተሰራ ሲሆን፣ በዚህ ሂደት ዛሬ የምትመረቁበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ (Autonomy) ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲደራጅ ተደርጓል። ሌሎች ዘጠኝ ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች የራስ-ገዝ ሂደታቸውን በሚቀጥለው አመት ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ተቋማቱ ከዩኒቨርሲቲ እውቀት ወጥተው በዘር፣ በመንደርና በጎሳ የሚያስቡበትን አደገኛ አሰራር ለመለወጥ፣ የዩኒቨርሲቲ አመራር ምደባ ከፖለቲካና ከዘር ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ የጸዳ ሆኖ በእውቀት፣ በብቃትና በግልጽ ውድድር ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን።

ውድ ተመራቂ ተማሪዎች፤ እናንተ ዛሬ የምትመረቁት በትምህርት ስርዓታችን ላይ የገጠመንን ስብራት ለመጠገን ሪፎርም በጀመርንበት ማግስት፣ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አስተዳደር የተወሰዱትን ጥብቅ እርምጃዎች አልፋችሁ በከፍተኛ ትጋትና ስኬት እዚህ የደረሳችሁ በመሆናችሁ ዕለቱን ልዩ ያደርገዋል። እናንተ የሪፎርሙ ጀማሪዎች እንደመሆናችሁ የነበረባችሁን ጫና ተቋቁማችሁ፣ በብቃታችሁና በልፋታችሁ ያገኛችሁት ውጤት በመሆኑ ስኬታችሁን የበለጠ ጣፋጭ ያደርገዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ወጥታችሁ ወደ ሰፊው የስራ አለም ስትቀላቀሉ፦

 1. ሁልጊዜም ተማሪ ሁኑ፦ ዲግሪ ስለያዛችሁ እውቀትን የጨረሳችሁ የሚመስላችሁ ሰነፎች ሳትሆኑ፣ ሁሌም በተጨማሪ ለመማር በትምህርት ቤቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተግባር ከማህበረሰቡ የሚገኘውን እውቀት ጨምሮ ከፍተኛ ፍላጎት ያላችሁ፣ ያንን እውቀታችሁንም ከሌሎች ጋር በማስተባበር ማህበረሰቡን በጋራ የምታሳድጉ ልባሞች እንድትሆኑ ሀገራችሁ ትሻለች። ለዚህም የኢትዮጵያን የወደፊት የረጅም ጊዜ ስልጣኔና ታላቅነት የሚመጥን አዲስ መንፈስ ያነገባችሁ ባለሙያዎች መሆን ይጠበቅባችኋል።

 2. ሙስናንና አድሎን ተጸየፉ፦ ከምንም በላይ ደግሞ ሙስናንና መሰል አድሏዊ አሰራሮችን የምትጸየፉ፣ ፍጹም ከእኩይ ተግባር በጸዳ መልኩ ሀገራችሁን የምትወዱና የምታገለግሉ፣ የራሳችሁ ህይወት መሻሻል ከሀገራችሁ መሻሻል ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን የምትረዱ የሀገሪቱ እውነተኛ ባለቤቶች እንድትሆኑ በዚህ አጋጣሚ አደራ ማለት እወዳለሁ።

 3. ሀገርን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፦ ኢትዮጵያ ከእናንተ የምትጠብቀው በዘመድ፣ በዘርና በአካባቢያዊ ጠባብ አስተሳሰብ የታጠረ አካሄድን ሳይሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሀገርን ማዕከል ያደረገ፣ ሀገሪቱን ወደፊት ለማስፈንጠር በኃላፊነት ስሜት የሚሰራ ትውልድ መሆኑን ነው። ይህንን ስንል መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ዛሬ ላይ የደረሱ የበለጸጉ ሀገራት እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸው ሳይሆን፣ የአንድና የሁለት ትውልድ ታላቅ መስዋዕትነት፣ እጅግ አስጨናቂ ጉዞና መከራን አልፈው ነው። በኛም ዘመን ይህንን ታላቅ ለውጥ እውን ለማድረግ የአንድ ትውልድ ዋጋ መክፈል ሊጠይቅ ይችላል።

 4. በትህትና ማህበረሰቡን አገልግሉ፦ እናንተ በዚህ አዲስ የትምህርት ስርዓት አልፋችሁ ስትወጡ "ከሌላው የተሻልን ነን" በሚል የትዕቢት ስሜት ሳይሆን፣ ይህንን ጥራት ያለው ትምህርት እንድታኙ ማህበረሰባችሁ ያደረገላችሁን ውለታና ታላቅ መስዋዕትነት በመረዳት፣ ከዚህ በተሻለ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ በቁርጠኝነት መስራት የምትችሉ የለውጥ አጋፋሪዎች እንድትሆኑ ነው።

 5. የፍትሃዊነትና የታማኝነት አምባሳደር ሁኑ፦ ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ የምትተጉ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል እንደ ወገናችሁ የምታዩ፣ እንዲሁም ከሙስናና አድሎ የጸዳችሁ የህዝባችሁ ታማኝ አገልጋዮች በመሆን የሀገራችንን ሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ የምታፋጥኑ የለውጥ መሪዎች እንድትሆኑ አደራ እላችኋለሁ።

በመጨረሻም፣ እናንተ የዛሬ ምርቆች ሀገራችን ደግሞ እህል የማትለምን፣ ልጆቿን በኩራት አብልታ ለአለም የምትተርፍ የፈጠራና የእውቀት ማዕከል እንድትሆን በምትሰማሩበት መስክ ሁሉ ለኩራትና ለፍትሃዊነት መረጋገጥ እንድትተጉ አደራ እላለሁ።

ለእናንተ ውጤት ማማር ሌት ተቀን ለደከሙ መምህራኖቻችሁና ለዛሬ ደስታችሁ እንድትበቁ ድጋፍ ላደረጉ ወላጆቻችሁ በታላቅ አክብሮት ምስጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።

በድጋሚ ለተመረቁ ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ፣ የወደፊት ህይወታችሁና ጉዟችሁ የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁ።

እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More

ተጨማሪ ዜናዎችን ያንብቡ

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ