የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ22 የምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የቀረቡ ዕጩዎችን ውጤት ይፋ ማድረጉን አስታወቀ። ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ያደረገው ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ላይ በስካይ ላይት ሆቴል በሚገኘው ጊዜያዊ ጣቢያው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በዚሁ መግለጫ መሠረት ቦርዱ ከአማራ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሦስት፣ ከኦሮሚያ ክልል ለክልል ምክር ቤት ዘጠኝ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት፣ እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ለክልል ምክር ቤት በሁለት የምርጫ ክልሎች ላይ የቀረቡ ዕጩዎችን ውጤት በይፋ አሳውቋል።
የምርጫ ውጤቱን ዝርዝር በተመለከተ፤ በአማራ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር በጎንጎን ምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲ በብቸኛነት ዕጩውን ያቀረበ ሲሆን፣ ከፍተኛውን ድምፅ ማግኘቱ ተገልጿል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት ምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል በሁሉም ምርጫ ክልሎች የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ከፍተኛውን ውጤት ማግኘታቸው ተመልክቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ቦርዱ በኦሮሚያ ክልል ለክልል ምክር ቤት በዘጠኝ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰባት የምርጫ ክልሎች መካከል ባካሄደው ውድድር፤ በሁሉም የክልል እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ከፍተኛ ውጤት ማግኘታቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል ለክልል ምክር ቤት ዕጩ በቀረበባቸው ሁለት የምርጫ ክልሎች፤ በሁለቱም አንደኛውን ከፍተኛ ውጤት የብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ያገኘ ሲሆን፣ በሁለተኛው የምርጫ ክልል ደግሞ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በዕጩነት ያቀረባቸው ተወዳዳሪ አራተኛውን ከፍተኛ ውጤት ማግኘታቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ያሳያል።