አምዶች

Logo ከይር ታይምስ

የዲጂታል ዜና እምብርት

የቅርብ ዜና
ነፃ ሃሳብ / እኔ እምለው

መንግስት ከሕዝብ እይታ የሸሸገውን የፋይናንስ ምንጭ በግልጽ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባል

በያፌት ግርማ | May 16, 2026

ከሰሞኑ በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደው “አዲሲቷ አዲስ አበባ” የውይይት መድረክ ላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ የተናገሩት ንግግር የከተማዋን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የኢኮኖሚ ባለሙያ ክፉኛ የሚያስደነግጥ ነው፡፡ 

የከተማዋ ዓመታዊ በጀት 350 ቢሊዮን ብር በሆነበት ሁኔታ፣ ለወንዝ ዳር ፕሮጀክት ብቻ 1.3 ትሪሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ይፋ ማድረጋቸው፣ በሀገሪቱ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የቅድሚያ ተዋረድ (Priority) እና በመንግስት ተጠያቂነት ላይ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ጥያቄዎችንና ጥርጣሬዎችን ይወልዳል፡፡ ይህ መረጃ የመንግስትን የልማት አቅጣጫ ብልሹነትና ስትራቴጂካዊ ስሀተት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ በጽኑ ሊተች ይገባዋል፡፡

የአንድ ከተማ አስተዳደር ዋነኛ ኃላፊነት የነዋሪዎቿን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ነው፡፡ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በከፋ የቤት እጥረት፣ በንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት፣ የትራንስፖርት ማነስ ችግር እና በኑሮ ውድነት እየተቆላች የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ 

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በቀን አንዴ መመገብ አቅቷቸው፣ ወጣቶች በስራ አጥነት እየማቀቁ፣ እና አረጋውያን የሕክምና አገልግሎት አጥተው በየሜዳው በወደቁባት ከተማ፤ ከዓመታዊ በጀቱ በአራት እጥፍ የሚበልጥ (1.3 ትሪሊዮን ብር) ለፓርክ እና ለወንዝ ዳርቻ ማስዋብ ፈሰስ ማድረግ የቅድሚያ ተዋረድን ሙሉ በሙሉ መሳት (Misplaced Priorities) ነው፡፡ 

ይህ “እህል ላበደረ ጠጠር” እንደሚባለው የሰነፎች አካሄድ ነው፡፡ ሕዝቡ ዳቦ በሌለበት ሁኔታ ንጹሕ አየር እንዲተነፍስ መጋበዝ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጨባጭ ስቃይ ካለመረዳት ወይም ሆን ብሎ ችላ ከማለት የሚመነጭ የቅንጦት እብደት ነው፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ ይህን ያህል ግዙፍ ገንዘብ “በመንግስትና በግል አጋርነት” (PPP) እና በባለሀብቱ ተሳትፎ የተገኘ ነው በማለት ለማድበስበስ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ ይህ ማብራሪያ ማኅበረሰቡን የሚያረካ ሳይሆን የባሰ ጥርጣሬን የሚጭር ነው፡፡

በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ 1.3 ትሪሊዮን ብር በግል ሴክተሩ በበጎ ፈቃድ ወይም በአጋርነት ፈሰስ ተደረገ ማለት ባለሀብቶች ይህንን ገንዘብ የሰጡት በነጻነት ነው ወይስ በባለሥልጣናት ቀጥተኛና ኢ-ቀጥተኛ ጫና (Coercion)? የሚለ ጥያቄ ያጭራል።

የመንግስት ባለሥልጣናት “ልማቱን ደግፉ” እያሉ የንግዱን ማኅበረሰብ የሚያስጨንቁበት ሥርዓት ባለበት ሀገር፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር በግል ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ የፍርሃት ድባብ ይፈጥራል፡፡

ይህ ግዙፍ ካፒታል ከባንኮች የተበደረ ከሆነ፣ የግሉ ዘርፍ ለአምራች ኢንዱስትሪ፣ ለግብርና እና ለንግድ የሚያገኘውን የብድር አቅርቦት (Crowding out effect) ሙሉ በሙሉ አድርቆታል ማለት ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት ለታየው የዋጋ ግሽበትና የሸቀጦች እጥረት ቀጥተኛ ተጠቃሽ ምክንያትም ነው፡፡

በማንኛውም ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ፣ ከመንግስት በጀት ውጪ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም የፋይናንስ ሞዴል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቅና ኦዲት ሊደረግ ይገባዋል፡፡ 1.3 ትሪሊዮን ብር (የሀገሪቱን የበርካታ ዓመታት የልማት በጀት የሚያክል ገንዘብ) ያለ ምክር ቤት እውቅና፣ ያለ ግልጽ ጨረታና የውል ስምምነት፣ በባለሥልጣናት መመሪያ ብቻ “ከየት መጣ ሳይባል” ወጪ መደረጉ የአስተዳደሩን ሕገ-ወጥነት ያሳያል፡፡ 

ይህ አሠራር ከተማዋን ወደ ግል ኩባንያነት የለወጠ፣ ተጠያቂነት የሌለው እና ሙስና በስፋት ሊደቀንበት የሚችል የተዘበራረቀ አሠራር (Shadow Economy) የፈጠረ ነው፡

ሌላው እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ፣ ይህንን አስደንጋጭ መረጃ የተናገሩት ራሳቸውን የኢዜማ ፓርቲ አመራር አድርገው የሚቆጥሩት አቶ ግርማ ሰይፉ መሆናቸው ነው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ብልሹ አሠራር፣ የፋይናንስ ብክነትና የሕግ ጥሰት መገሰጽና መቆጣጠር ሲገባቸው፣ በተቃራኒው የመንግስት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሕዝብን ቅሬታ ለማስተባበልና ይህንን የመሰለ አስደንጋጭ የፋይናንስ መዛባት “እንደ ትልቅ ስኬት” ለመግለጽ መሞከራቸው የፖለቲካ ሥነ-ምግባር ውድቀትን ያሳያል፡፡ ይህ የሚያሳየው ተቃዋሚዎች የመንግስት ሥልጣን ፍርፋሪ ሲያገኙ የቆሙለትን መርህና የሕዝብን ወገንተኝነት እንዴት በቀላሉ እንደሚዘነጉ ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት ስም የተደረገው 1.3 ትሪሊዮን ብር ወጪ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት መሠረታዊ በሆነ መልኩ የማይቀይር፣ ይልቁንም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጤናማነት አደጋ ላይ የጣለ “የስም ዝና” ናፋቂ ፕሮጀክት ነው፡፡

መንግስት ከሕዝብ እይታ የሸሸገውን የፋይናንስ ምንጭ በግልጽ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ፣ የፌዴራል ኦዲተር መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ ሊያደርግና የተዛባው የልማት ቅድሚያ ተዋረድ በአስቸኳይ ወደ ነዋሪው መሠረታዊ ፍላጎት (ወደ ምግብ ዋስትና፣ ቤትና ውኃ) ሊመለስ ይገባል፡፡ ማሸብረቅና ማስዋብ ያለበት የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እንጂ የባለሥልጣናት የፎቶ ማሳያ የሆኑት የወንዝ ዳር ዳርቻዎች ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More

ተጨማሪ ዜናዎችን ያንብቡ

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ