አምዶች

Logo ከይር ታይምስ

የዲጂታል ዜና እምብርት

የቅርብ ዜና
ነፃ ሃሳብ / የክይር እንግዳ እ.ኤ.አ.: May 14, 2026

የቀይ ኩሬው ምስጢር እና የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ

አሰብ የማን ነው? የባህር በር ጥያቄ አሁን ለምን ተነሳ? የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪው ዕይታ

ወደብ ስለሌለህ ብቻ ደሃ ትሆናለህ ማለት አይደለም፤ ወደብ ስለአለህ ደግሞ የግድ ሀብታም ትሆናለህ ማለትም አይደለም። ኤርትራ ከአንድም ሦስት ደሴቶችና ሁለት ወደቦች አሏት፤ ግን ኤርትራ ዛሬ የት ደረሰች? መንግስት ያነሳው ጥያቄ መሰረታዊ ነው፣ በዚህ ላይ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያስፈልገናል። አሰብ ላይ ያሉት አፋሮች ናቸው፤ በመሰረቱም አሰብን የመሰረቱት አፋሮች ናቸው። በአፋርኛ "አሰቡይ" ማለት "ቀይ ኩሬ" ማለት ነው። የኢትዮጵያ የባህር በር ግንኙነት የሚጀምረው ከቅድመ አክሱም ስልጣኔ በፊት ነው።

ከይር፦ የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪና ፖለቲከኛ እጩ ዶክተር ትእግስቱ አወሉ እዚህ ስቱዲዮአችን ተገኝተውልናል። ጊዜዎን መስዋዕት አድርገው ስለመጡ እጅግ በጣም ከልብ አመሰግናለሁ። ከታሪካዊ ምህዳሩ እንነሳና ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት ከዘመናት በፊት የቆየ ነው። እስኪ ይህ ታሪክ የዛሬውን የባህር በር ምኞት እንዴት ሊመለከተው እንደሚችል በአጭሩ ቢገልጹልኝ? እንዲሁም ታሪካዊ የድንበር ክልሎች ለዛሬው የወደብ መዳረሻዎች ለሚፈጥሩ ተግዳሮቶች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ምንድነው ይላሉ?

ትዕግስቱ፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ነገርን ከስሩ ማንሳት መልካም ስለሆነ፣ እንግዲህ የኢትዮጵያ የባህር በር ግንኙነት የሚጀምረው ከቅድመ አክሱም ስልጣኔ በፊት ሲሆን፣ ከቅድመ አክሱም ስልጣኔ በፊት ጎልቶ ይታይ ከነበረው የዳማት ስልጣኔ ነው። እንግዲህ የዳማት ስልጣኔ የራሱ ዋና ከተማ ያለው ሲሆን፣ በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል "የሃ" የሚባለው የዳማት ዋና ከተማ ነበረ። በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኔም ሆነ የጥንታዊ ስልጣኔዎች እና የመንግስት አመሰራረቶች በታሪካዊ ትምህርቱ የተለያዩ ዘርፎች አሏቸው። አንዱ ንግድ ነው። ሌላው ሃይማኖት ነው፣ የሃይማኖትም ትስስር አለ፤ ሌላው ደግሞ በወታደራዊ ሁኔታ ነው። እነዚህ አራት ነጥቦች አሉ። ስለዚህ ከዛ አንጻር ስንነሳ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ግንኙነት የሚጀምረው ከዛ ነው።

ይሁንና በተለይ የአክሱም ስልጣኔ ከሦስት ክፍለ ዘመን ማለትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የአክሱም ስልጣኔ እየጎለበተ የመጣበት ዘመን ነው። አክሱም ደግሞ የሚታወቀው በረጅሙ የንግድ ትስስር ነው። በተለይ በወቅቱ ከግሪክና ከሮማን ታሪክ ጋር ይገናኛል። ንግዱም የኤክስፖርትና የኢምፖርት የንግድ ልውውጥ የነበረው ነው። ይህንን ሲያደርግ የአክሱም ከፍተኛ መተላለፊያ የነበረው በቀይ ባህር ዳርቻ በኩል ሲሆን፣ በቀይ ባህር ውስጥ የአዱሊስን ወደብ የአክሱም መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ይቆጣጠረው ነበር። ከዛ ጀምሮ ወደ ሌሎችም ወደቦች፣ ምናልባት አሁን ሶማሊላንድ የምንለው ራሱ እስከዛ ድረስ የንግድ ሂደቱን ሲያስኬድ የነበረ ነው። ግንኙነታችን ብቻ አይደለም፤ በቀይ ባህር ውስጥ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርግ የነበረ መንግስት ነው።

ከሦስተኛው ክፍለ ዘመን እስከ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተለይ የአክሱም ስልጣኔ እየተዳከመ ሲመጣ ነው ነገሮች የቀሩት። እና ቀይ ባህርን ስንወስደው፣ በዛኛው ቀይ ባህርና በዚህኛው ቀይ ባህርበዚህኛው ቀይ ባህር አክሱም ይቆጣጠራል። ከዛም ተሻግሮ ሳውዲ አረቢያ በሚባለው አካባቢና በየመን በኩል እያስተዳደረ፣ አክሱም በተለይ በዘመነ ካሌብ ጊዜ ለምሳሌ ሹመት የሰጠበት ሁኔታዎች አሉ። የቀይ ባህር ተዋናይ ነን የሚሉ ዛሬ የምናያቸው ኃይሎች በወቅቱ ራሳቸውን እንኳን በመንግስትነት የማያውቁ ህዝቦች ነበሩ። በርግጥም ጠንክረው ባልወጡበት ሁኔታ አክሱም አካባቢውን ይቆጣጠር ነበር።

በዛን ዘመን አክሱም ከአራቱ የዓለም ታዋቂ ወይም ኃያል ከሚባሉ ሀገሮች አንዱ ነበር። አንደኛው ፐርሺያ ሲሆን፣ ቀጥሎ የሮማን ኢምፓየር ነው፣ ከዛም አክሱም ራሱ ነው። ስለዚህ አክሱም ከአራቱ አንዱ የነበረ ስልጣኔ ነው። አዱሊስ የንግድ መለዋወጫ ብቻ ሳይሆን የባህር ንግድ ይካሄድበት የነበረ፣ ከዛም አልፎ የመርከብ ጥገና የነበረበት ነው። የንግድ መርከብ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ የወታደራዊ ባህር ኃይል መርከብ የሚሰራበት የነበረ ነው። ስለዚህ ይህ ታሪካዊ ዳራ ነው።

በአክሱም ስልጣኔ ከአክሱም ወደብ ጋር ከነበረን ግንኙነት በኋላ፣ ሌሎች እነ ኦቶማን ተርኪ የመሳሰሉት አካባቢውን ሲቆጣጠሩ እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያ ከወደብ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጣች የመጣችው። እንጂ በመሃልም የጣሊያን ጭምር አለ፤ ከአሰብ ተነስቶ የሄደበት መንገድ እሱም የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። ከዛም በኋላ ደግሞ ከፌዴሬሽኑ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ነገር አለ፤ በተለይ አሰብና ምጽዋ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ነበር። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ነበርን። አዱሊስን በፈረንጆቹ አቆጣጠር 702 ዓመተ ምህረት አካባቢ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ እስልምና ጠንክሮ መምጣቱ አዱሊስን የመታውና ያፈረሰው በዛ ዘመን ነው። ከዛ በኋላ እየተዳከመ መጣ፤ በውስጥም የፖለቲካ ጉዳይ ስለነበረ ወደ ውጪ ለማየት ነገሮች እድል አልተሰጣቸውም።

ስለዚህ በምስራቁ በኩል ያለውን ዘይላ የሚባለውን በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል ያለውንም ጨምሮ ይቆጣጠር የነበረው የኢትዮጵያ ግዛት ነው። ማለት ከቀይ ባህር ዳርቻ እስከ የብስ በኩል ያለው ርቀት እንኳን 300 ኪሎ ሜትር ነው። የታሪክ ዳራችን ከወደብ ጋር ነው፤ ምክንያቱም አክሱም የሰለጠነው በባህር ላይ ንግድ ነው። በየብስና በባህር ኤክስፖርትና ኢምፖርት በማድረግ፣ በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያውን ገንዘብ ያተመው አክሱም ነው። ሳንቲም ያተመው አክሱም ነው፣ ያውም ከወርቅ፣ ከነሐስና ከብር። ስለዚህ የኢንተርናሽናል ግንኙነት በዛ ልክ ነበር የሚካሄደው። ኤክስፖርት አለው፣ ኢምፖርት አለው፤ ከአውሮፓም፣ ከእስያም ከሌሎችም ሀገሮች ጋር ግንኙነት ነበረው። እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የነበረው ግንኙነት ከዚህ ከአዱሊስ ተነስቶ የነበረ እንቅስቃሴ ነው። በአጭሩ ይህን ይመስላል።

ከይር፦ የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪና ፖለቲከኛ እጩ ዶክተር ትዕግስቱ አወሉ፣ እየሰጡን ስላለው ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ። ወደ አሁኑ እንመለስና የባህር ተደራሽነት ጥያቄ አሁን ለምን በጣም እየጠነከረ መጣ? ይህንን አዲስ ግፊት የሚያባብሱ የትኞቹ የጂኦ-ፖለቲካ አዝማሚያዎች ናቸው?

ትዕግስቱ፦ አንድ ነገር ማየት አለብን። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ነው የምትገኘው። አፍሪካ ቀንድ ደግሞ በተለይ የኦቶማን ተርኪ ከወጣ በኋላ፣ የእሱን ፈለግ ተከትሎ በርካታ ጣልቃ ገቦች ያሉበት ቦታ ሆኗል። አፍሪካ ቀንድ አራት ሀገሮች ናቸው። አሁን በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ አራተኛዋ ሆናለች። ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ። ነገር ግን እነዚህ ኃያላን የሚባሉት ጣልቃ ገቦች ሲፈልጉ "ታላቁ የአፍሪካ ቀንድ" የሚል ስያሜ በመስጠት ሌሎችንም ያካትታሉ፤ ይህም ከራሳቸው የጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎት አንጻር ነው።

ይህ ጥያቄ አንደኛ ነገር ሦስት ዋና ዋና የባህር ንግድ መስመር ያለባት ቦታ ስለሆነች ነው። ቀይ ባህር አለ፣ የኤደን ባህረ ሰላጤ አለ፣ የባብ-ኤል-መንደብ መተላለፊያ አለ። ይህ ማለት አውሮፓን ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የሚያገናኝና በዓመት ውስጥ በከፍተኛ መጠን የሚቆጠር ቶን መርከብ የሚተላለፍበት ነው። በጂኦ-ፖለቲካ ሲታይ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛቷ አንደኛ ስትሆን፣ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ 130 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ሁለተኛ ስፍራን ይዛለች። ስለዚህ ይህ አንድ ጉዳይ አለ። ሁለተኛው ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ ያለው የግብፅ ፍላጎት ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ችግሮች ምን ጊዜም መነሻቸው የውስጥ የሚበጠብጠው ሁኔታ ነው። የቀይ ባህር ጉዳይ አሁን ጎልቶ ወጣ እንጂ ጥያቄው ድሮም የነበረ ነው።

በኢህአዴግ ጊዜ ሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች የቀይ ባህርን ጥያቄ ያነሱ ነበር፤ ኢህአዴግ ግን አላነሳውም፣ ወይም ፍላጎቱ አልነበረውም፤ ይህ በራሱ ምክንያት ነው። ግን እኛም የፖለቲካ መሪዎች በነበርንበት ጊዜ ውስጣችን ይህ ጥያቄ ምንጊዜም አለ። ከጊዜ መርዘም ጋር ተያይዞ ዝም የተባለ ቢሆንም ማለት ነው። ሁለተኛ ነገር፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በናይልና በቀይ ባህር ላይ ያጠነጠነ ነው። ግብፅ የዚህ ከፍተኛ ተዋናይና የድራማው ደራሲ ነች። የኤርትራ መገንጠል በራሱ ከኢትዮጵያ የቀይ ባህር ማሳጣት ጋር የተያያዘ ነው። የኢትዮጵያ አቅም ቀላል አልነበረም። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የራሷ ችግር ስላለ ነው እንጂ፣ በኢኮኖሚ የተሻለ ብትሆን ኢትዮጵያ በቀጠናው ኃያል ልትሆን እንደምትችል እገምታለሁ። በትክክልም ተሰሚነት አላት፣ ይህም ታሪካዊ ነው። ምክንያቱም በኮሎኒያሊዝም ጊዜ ፀረ-ኮሎኒያሊዝም እንቅስቃሴን የበለጠ ስታጠናክር የነበረችና ለአፍሪካ ነጻነት የታገለች በመሆኗ አሁንም ትደመጣለች። ነገር ግን አሁን ለመደመጥ የተቸገረችው በኢኮኖሚ፣ በሰላም ጉዳይ እና በሌሎች የዲፕሎማሲ ችግሮች ምክንያት አሁን ያለው ጥንካሬያችን ተዳክሞ ስለሚሆን ነው። ስለዚህ እነዚህ ኮሎኒያሊስቶች ዋና ግባቸው ኢትዮጵያን የበለጠ ማዳከም ነው።

ይህ ደግሞ ጥቅሙ ለአረቡ ዓለም ነው። እንደምታየው የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት ስለሆኑ። ነገር ግን ግብፅ የምትሰራቸው ስራዎች አሉ። ከድሮ ጀምሮ የኢትዮጵያን ጎልቶ መውጣት አትፈልገውም፤ በእሷ እምነት ሊሆንም አይችልም። አንዳንዴ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ያስመስላሉ፤ ዞሮ ዞሮ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የተመላለሱት ገዢዎች፣ በተለይ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ፣ ከእነዚህ ሀገሮች ጋር ግንኙነት እያደረጉ ነው የመጡት። በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን የሚመጡትን የሻቢያንና ሌሎችንም የሚያሰለጥኑት በጎረቤቶቻችን ሀገሮች ነው። ለምሳሌ ሱዳን አንዷ ነች። የአረቡ ሀገሮች እነ ሶሪያ የመንግስትን ተቀናቃኞች ወስደው የሚያሰለጥኑበት ሁኔታዎች ነበሩ። ይህ ከድሮ ጀምሮ የነበረና አሁንም ያለ ነው። ይህ የእነሱን ፍላጎት ለመጠበቅ ነው።

ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? ጠንካራ እየሆንክ ከመጣህ ምንጊዜም ጠንካራ ነህ፤ የምትፈልገውን ጥያቄ በዲፕሎማሲም ቢሆን ማስከበር ትችላለህ። አቅም ሲኖርህ ነው የምትናገረው የሚሰማው። አቅም ሳይኖርህ ሲቀር የፈለከው መልካም ነገር ቢሆንም አድማጭ አይኖርህም። ስለዚህ ዲፕሎማሲ ከውስጥ ጥንካሬ ጋር ነው የሚሄደውከኢኮኖሚና ከወታደራዊ አቅም ጋር ተያይዞ። ኢኮኖሚ ሲያድግ ወታደራዊ አቅምም አብሮ ያድጋል። ምክንያቱም ምንጊዜም የፍላጎት ግጭት አለ። ይህ ክርክር በአካባቢው በየብስም ይሁን በባህር ተጋሪ ሀገሮች መካከል አለ። በመካከላቸው የመስማማት ነገር ቢኖር መልካም ነበር፤ ነገር ግን ለምሳሌ ሶማሌዎች ኢትዮጵያን የሚስሏት በአፍሪካ ቀንድ ያለች "እስራኤል" አድርገው ነው። የእስልምና ተከታዮች ኢትዮጵያን ከጥንት ጀምሮ "የክርስቲያን ደሴት" ብለው ነው የሚጠሯት፤ ይህንንም ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀሙበታል።

የወደብ ጥያቄ ከታሪክም ሆነ አሁን ከደረስንበት ደረጃ፣ በተለይ ከዲፕሎማሲ አንጻር አስፈላጊ ነው። ጥያቄው የተነሳበት መንገድና ይህን ለማስፈጸም የምንሄድበት ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ። ምክንያቱም ሁልጊዜ በፖለቲካ አንድ ነገር ስታስቢ፣ አንቺ ከምታራምጂው የፖለቲካ አቅጣጫ ጋር ነው ጥያቄ የምታነሺው። በፊት ለምንድነው 27 ዓመታት ጥያቄ ያልተነሳው? ኤርትራና ኢትዮጵያ 20 ዓመታት ተዘጋግተው የነበሩ ሀገራት ናቸው። ዝግ የሆነ ፖሊሲ ነበር የተከተሉት። የነበረ ጦርነትም የለም፣ ሰላምም የለም፤ ግን አንድ ቀንም የመንግስት ሰዎች ስለወደብ ጥያቄ አንስተው አያውቁም ነበር።

አሁን ደግሞ ጥያቄው ለምን ተነሳ ሲባል የፖለቲካ ጉዳይ ነው። ጥያቄው ትላንት አልተነሳም፤ ያኔም የነበረው ህዝብ ነው፣ አሁንም ያለው ህዝብ ያው ነው። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆናለች። አሁን ማለት ግን አንዳንድ ሰው ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ነገር፣ በእኔ እምነት ወደብ አልባ ስለሆንክ ደሃ ትሆናለህ ማለት አይደለም፣ ወደብ ስለአለህ ደግሞ ሀብታም ትሆናለህ ማለትም አይደለም። ኤርትራ ከአንድም ሦስት ወደቦችና ወደ ሁለት ደሴቶች አሏት፤ ነገር ግን ኤርትራ አሁን የት ደረሰች? ሶማሊያ ብዙ ወደብ አላት፤ የት ደረሰች? በሌላ በኩል ደግሞ ወደብ የሌላቸው ሀገሮች አውሮፓ ውስጥ አሉ። ግን ለህዝባቸው መነሻ አድርገው በማሰብ፣ ባለው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሀገራት ጋር በመስማማት የባህር በር ፍላጎታቸውን የመለሱበት ሁኔታ አለ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እንደመሆኗ መጠን በወደብ ሀብታም በሆኑ ሀገሮች ተከባለች። አፍሪካ ቀንድ ስንል ወደብ ያላቸው ሀገራት ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ኤርትራ ናቸው። በእነዚህ ሀገራት የተከበበች ብትሆንም ግን ዛሬም ወጪ እያወጣች ነው። ምናልባት ይህ ኢኮኖሚያዊ ምልከታ ሊሆን ይችላል፤ እኔ ግን ከኢኮኖሚውም በላይ የደህንነቱ ጉዳይ ያሳስበኛል። ይህን ትኩረት የምሰጠው በኢኮኖሚ ያደግን ብንሆን እነዛ ሀገሮች ከእኛ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይችሉ ነበር፣ ፍላጎታቸውን እናቅርብላችሁ ይሉ ነበር። የደህንነት ጉዳይ ስንል እነዚህ ወደብ ያላቸው ጎረቤቶቻችን በከፋቸው ጊዜ ምንም ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። በኢኮኖሚውም ወጪ ገቢውን ሊዘጉብን ይችላሉ፤ ከዛም በላይ እድገታችንን ሊገቱብን ይችላሉ። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ እኛ የንግድ እንቅስቃሴያችንን በባህርና በየብስ ካልቻልን በአየር እንዲሆን እንገደዳለን፤ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህን ማስፈራሪያዎች እያደረጉ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ አቅሙ አለው፣ በዚህ ላይ ምንም ጥርጥር የለውም፤ አሁን የሌለው ፖለቲካው ነው። ፖለቲካው ጥሩ አይደለም።

አሁንም ደግሞ ይህ የወደብ ጥያቄ መንግስት ያነሳው ጥያቄ መሰረታዊ ነው፣ ጥርጥር የለውም ያስፈልገናል። በምን አይነት መንገድና በምን አግባብ ያስፈልገናል የሚለው መጠናት ያለበት ጉዳይ ነው። ነገር ግን ጥያቄ መነሳቱ በአንድ በኩል፣ እኔ እንደ አንድ የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪ ስረዳው፣ ዓለም አቀፍ ጆሮ አግኝቷል። ውጤቱ ምን ይሁን ምን ጆሮ ይዟል። በዚህ ዘመን ይሁን በሚቀጥለው ዘመን አናውቅም፤ ግን ጥያቄው አለ። ለምሳሌ ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ጥያቄ ጥንታዊ ነው።

የአካባቢያችንን የጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት ኢትዮጵያ የምትቀርበው ለጅቡቲ ነው። ነገር ግን 10 በላይ ሀገሮች ጅቡቲ ላይ ወደብ መስርተዋል። አዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ ሀገሮች በሊዝ ተከራይተው ነው የሚከፍሉት። ክፍያው በዓመት ቢሰበሰብ 300 ሚሊዮን ዶላር ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ በወጪና ገቢ የወደብ አገልግሎት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። የጅቡቲ ዓመታዊ ገቢ እስከ አራት ቢሊዮን ይገመታል፤ በሌላ አነጋገር 50 በመቶ የሚሆነውን የምትሸፍነው ኢትዮጵያ ነች።

ሁለተኛ ነገር፣ ጅቡቲ በአሁኑ ሰዓት ንጹህ የመጠጥ ውሃ የምታገኘው ከኢትዮጵያ ነው። ጅቡቲ በሁለት ብሄረሰቦች ላይ የቆመች ነች፤ አንዱ ሶማሌ ነው፣ ሌላው አፋር ነው። አናሳው አፋር ሲሆን አብላጫው ሶማሌ ነው። ሶማሌም ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፤ አፋርም ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። ይህን ስንመለከተው ከፍተኛ ትስስር ያለው ሀገርና ህዝብ ነው። ለጥሩም ለመጥፎም ይህ ትስስር ሊረዳ ይችላል። በመሆኑም ጂኦ-ፖለቲካው ቀላል አይደለም። ሌላው ነገር አሰብን አፋሮች ናቸው የመሰረቱት። ለምሳሌ "አሰብ" የሚለው ቃል በአፋርኛ ትርጉሙ "አሰቡይ" ማለት ሲሆን፣ በአማርኛ "ቀይ ኩሬ" ማለት ነው። በአፋርኛ ቋንቋ ይህ ራሱ የሚያመለክተው አሰብን የመሰረቱት አፋሮች መሆናቸውን ነው።

ነገር ግን በተለያየ ጊዜና ሁኔታ፣ አንዴ የኢትዮጵያ ግዛት፣ በሌላ ጊዜ ከኤርትራ ጋር እየተደረገ አስተዳደራዊ አደረጃጀቱ በዛ መንገድ ሲሄድ ቆይቷል። መጨረሻ ላይ ግን አሰብ "ራስ-ገዝ" ተባለ። በወቅቱ "አፋር" ማለት ይቻላል ነበር፤ ግን የነበረው ስርዓት የጎሳ ስያሜ መስጠት አልፈለገም፤ ልክ እንደ ኦጋዴን ራስ-ገዝ እንዳለው። እኔ ራሴ የማውቀውና ያየሁት ነው፤ ለኢትዮጵያ ያሉት ወደቦች ሁሉ ቅርብ ናቸው። ከወደቦቹ ውስጥ አንደኛው ታጁራ ሲሆን፣ ሁለተኛው አሰብ፣ ሦስተኛው ደግሞ በአሰብና በታጁራ መካከል ያለው ሃሌብ ደሴት ነው። አሰብን ከመቆጣጠር አንጻር በወቅቱ በነበሩት መንግስታት ትንሽ ግጭት ነበራቸው። እዛ ያለው ትግርኛ ተናጋሪና እዚህም ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ምንም ልዩነት የሌለው ህዝብ ነው። የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲክስ ሁሉንም የቀንዱ ተጋሪ ሀገሮች ህዝቦች በውስጧ የያዘች ሀገር ነች።

ከይር፦ የጂኦ-ፖለቲካ ተመራማሪና ፖለቲከኛ እጩ ዶክተር ትዕግስቱ አወሉ፣ እየሰጡን ስላለው ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እንዲሁም ግብፅ ጋር ካላት ግንኙነት አንጻር የዛሬ የባህር በር ጥያቄዋን እንዴት ይመለከቱታል? አያይዘውም ቻይና፣ አሜሪካ እና ሩሲያ በአካባቢው ያላቸው ተሳትፎ ሲያሳድጉ እያየን ነው፤ ዓለም አቀፍ ኃያላን ሀገራት በኢትዮጵያ የባህር ስትራቴጂ ላይ ምን ተፅዕኖ ያደርጋሉ ብለው ያስባሉ?

ትዕግስቱ፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። አሁን ሦስቱ ጎረቤቶቻችን ሀገራት ወይም የቀንዱ ተጋሪ የሆኑት ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ እንደሚታወቀው የአረብ ሊግ ተሳታፊዎች ናቸው። በሌላ መንገድ ደግሞ የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገሮች ህብረት ለዚህ ስትራቴጂ ብለው ያወጡት ነገር አለ። የግብፅን ሀሳብ ለመደገፍ በሰሞኑ የባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ያሉ አምስት ሀገሮች አሉ። ዮርዳኖስን ጨምሮ ኤርትራ መኖሯን በቂ መረጃ የለኝም፤ ነገር ግን ቀይ ባህርን ያለማስነካት ሀሳብ የደገፈ ነው።

ለዚህም ትልቁን ሚና ወስዳ የምትጫወተው ሳውዲ አረቢያ ናት። ቀይ ባህርን ከመከላከል አንጻር፣ በተለይ የግብፅን ፍላጎት ለማሟላትና በቀይ ባህር ለመጠቀም፣ አሁን ላይ ጥሩ የሚባል ግንኙነትን ከኤርትራ ጋር ፈጥረዋል። በአንድም በሌላ መልኩ ቢሆን ሀሳቡ ኢትዮጵያን በብዙ ነገር ማዳከም ነው። አንደኛ ነገር በጦርነት እንኳን ደፍረው ቢመጡ፣ ደህንነታችንን በተመለከተ መሳሪያዎችን ማስገባት አንችልምበእነሱ አልፎ የሚመጣ ከሆነ፤ ወይም በውድ ዋጋ በአየር ላይ መጠቀም ይሆናል የምንችለው። በሌላ መንገድ በቀስታ፣ ሳይታወቅባቸው፣ እንዳይገባ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሁለተኛው ነገር እዛ አካባቢ ያሉትን አቅሞች እንዳይታዩ በማድረግ ነው፤ በተለይ አዲሶቹ እነ ሳውዲ አረቢያ እና ኤምሬትስ የሚፎካከሩበት ቀጠናም ሆኗል።

ሌላው፣ ያደጉ ነባር ሀገራት ጦርነት አያስፈልግም እያሉ ሀሳባቸውን ቢገልጹም፣ ቱርክን ጨምሮ ትልልቅ የመሳሪያ አምራች ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉት በህጋዊ ወይም በህገ-ወጥ የመሳሪያ ሽያጭ ላይ ነው። ስለዚህ እዚህ አካባቢ ሽያጭ እስካለ ድረስ ጦርነት ይኖራል። በቀጠናው ጦርነት የሌለባት አንፃራዊ ሀገር ጅቡቲ ብቻ ናት፤ እሷም ቢሆን በአፋር ጉዳይ ትንሽ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመግባባት ይታይባታል። ሶማሊያም፣ ኢትዮጵያም እና ሱዳንም ቢሆኑ ችግር ውስጥ ያሉ ሀገሮች ናቸው። ስለዚህ ጦርነት ለእነሱ ገበያቸው ነው።

ለምሳሌ ሶማሊያ ውስጥ እነዚህ አረብ ሀገሮችሳውዲ አረቢያ እና ኤምሬትስአካባቢውን ለመቆጣጠር የጦር ካምፕ በመስራትና የጦር ልምምድ በማድረግ ጦርነት ያዘጋጃሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጦርነቱ የሚፈጠረውን ችግር ለማከም ሆስፒታሎችን ይከፍታሉ። እንጂ ትምህርት ቤት ከፍቶ የሶማሊያ ልጆች እንዲማሩ እናድርግ ብሎ የሚያስብ የለም። የህክምና ቦታ ነው እንጂ ትምህርት ቤት ተከፍቶላቸው የሶማሌ ልጆች እንዲማሩ የሚያደርግ የለም፤ እኔ ራሴ ያየሁት ነው። እነዚህ ኃይሎች፣ አዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ፣ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ነው።

የአሰብን ድንበር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፤ በእግር መሄድ የሚቻልበት 57 ኪሎ ሜትር የሆነ የድንበር ቦታ ነው። ሌላው የታጁራ ወደብ ግማሹ ነዋሪው አፋር ነው። ይህ ማለት ከኢትዮጵያ አፋር ክልል ጋር የተቆራኘ ነው። ትስስሩ ቢጠናከር ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ነው። አሰብን በዲፕሎማሲም በነበረን ሁኔታም መጠቀም የምንችልበት እድል አለን። ከጅቡቲ ይልቅ ከኤርትራ ጋር ካለው ቅርበት አንጻር፣ በኢኮኖሚውና በህዝቡ አንድነትበአንድ ወቅት ተለያይተው የነበረ ቢሆንም እርስ በእርስ ድጋሚ የመገናኘቱ ሁኔታ ሲፈጠር የህዝቡን ደስታ አይተነዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በጂኦ-ፖለቲካው ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ተጋሪ ሀገራት ተወካዮች አሉ። ኤርትራ ውስጥ የሚነገረው ትግርኛ እዚህም ይነገራል፤ ሶማሊያ ክልል ፈጥረዋል፤ ጅቡቲና አሰብ ላይ ያሉት አፋርኛ ተናጋሪዎች እዚህ ክልል አላቸው። ስለዚህ መታየት ያለባቸው እነዚህ ነገሮች ናቸው።

የቀይ ባህር በር ጥያቄ ዛሬ ሊመለስ ይችላል፣ ወይም የዛሬ 10 ዓመት፣ ወይም የዛሬ 100 ዓመት ሊመለስ ይችላል፤ አይታወቅም። ነገር ግን ግብፅ የአባይን ጉዳይ በተመለከተ ተጠቃሚነቷን በህገ-መንግስቷ እንዳስቀመጠችው፣ እኛም ማድረግ አለብን። ምክንያቱም ማንም ቢመጣ የራሷን ዕድል በመጠበቅ፣ ህገ-መንግስታዊ አቅጣጫን መሰረት በማድረግ የሚመጣው አመራርም ሆነ ገዢ ፓርቲ ሊተገብረው ግድ የሚል የተቀመጠ ህግ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያም የባህር በር ጥያቄዋን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ አለባት። ጦርነት ለማንም ስለማይጠቅም፣ ምክንያት እንጂ ድል ስላልሆነ፣ ከጦርነት በኋላ የሚመጣው ድርድር በአሸናፊና ተሸናፊ ስሜት መካከል ስለሚሆን ጠቃሚና ፍትሐዊ አይሆንም። ስለዚህ በሰላማዊ መንገድ መሆኑ ግድ ነው። በሌላ መልኩ፣ ኃያላን ሀገራት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር እንደመሆኗ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ላይ የነበራትን አቋም እና ተግባር በመቃወም ከዘመን ዘመን ተሸጋጋሪ ቂም ሊኖራቸው ይችላል። ዲፕሎማሲ ስለሆነ ከላይ ከላይ ሊወራ ይችላል፤ ግን ኢትዮጵያ ከበረታች አፍሪካን የመቆጣጠር አቅም አላት። ስለዚህ በተቻለ መጠን በስምምነት ቢያልቅ ይሻላል ብዬ ነው የማምነው፤ ጦርነትን አላበረታታም።

 

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More

ተጨማሪ ዜናዎችን ያንብቡ

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ