አምዶች

Logo ከይር ታይምስ

የዲጂታል ዜና እምብርት

የቅርብ ዜና
ዜና / የሀገር ውስጥ ዜና እ.ኤ.አ.: May 9, 2026

«ልመና በቃን፤ ወደ ቀድሞ ቀያችን ተመልሰን ራሳችንን መርዳት እንፈልጋለን» - ተፈናቃዮች

ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ጃርቴ ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የሰፈሩ ወገኖች፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በከፋ ሁኔታ ውስጥ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ተመልሰው ራሳቸውን እንዲረዱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቀረቡ።

በደቡብ ወሎ ዞን በጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለጋዜጣው እንደገለጹት፤ ለዓመታት በእርዳታ እጅ መጠበቅ ለስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጓቸዋል። «ጥያቄያችን ግልጽ ነው፤ ወደ ተወለድንበትና ወደ አደግንበት ቦታ መልሱን፤ ሰርተን ራሳችንን እንደግፍ፤ ልመና በቃን» ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል። ተፈናቃዮቹ አክለውም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የጸጥታና የመሠረተ ልማት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመልሷቸው በፅኑ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሰርካዲስ አታሌ በበኩላቸው፣ በመጠለያ ጣቢያና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ወገኖችን የመመለስ ጉዳይ በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል። «ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አከናውነናል» ብለዋል።

ሆኖም ምክትል ኮሚሽነሯ አያይዘው እንደገለጹት፤ መንግሥት ሁሉንም ተፈናቃዮች የመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም፣ የተመላሾችን ደህንነት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ማረጋገጥ ቀዳሚውና ወሳኙ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል። የጸጥታ ሁኔታው ተፈትሾና ተመላሾች በሰላም መኖር የሚችሉበት ሁኔታ ሲረጋገጥ የመመለስ ሂደቱ እንደሚፋጠን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኦሮሚያና ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎና በሰሜን ወሎ ዞኖች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ64 ሺህ በላይ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ተፈናቃዮቹ አሁንም በቂ ሰብአዊ እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነና ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት እንዲያስከብር ተማፅነዋል።

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More
ዜናውን ያጋሩ:

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ