አምዶች

Logo ከይር ታይምስ

የዲጂታል ዜና እምብርት

የቅርብ ዜና
ፖለቲካ / ዲፕሎማሲ እ.ኤ.አ.: May 9, 2026

ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቿ ደኅንነት እንዲጠበቅ ጠየቀች

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፣ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደኅንነት ዙሪያ በአዲስ አበባ ከደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንኬባ ሎሲ ጋር ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ተወያዩ። ይህ ውይይት የተካሄደው በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች በውጭ ዜጎች፣ በተለይም በኢትዮጵያዊያን ፍልሠተኞች እና ነጋዴዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች ማገርሸታቸውን ተከትሎ ነው።

ሚንስትር ደዔታ ብርሃኑ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና የማንገላታት ድርጊቶች የኢትዮጵያን መንግሥት በእጅጉ አሳስበውታል። የዜጎች ደኅንነት መከበር ለኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፣ መሰል ጥቃቶች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳያሻክሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"በቅርቡ በውጭ ዜጎች እና በወገኖቻችን ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች እጅግ አሳሳቢ ናቸው" ያሉት ሚንስትር ደዔታው፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የኢትዮጵያዊያንን ደኅንነት ለመጠበቅ እና መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ጠንካራ እና ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ንብረት እንዳይዘረፍ እና ህይወታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የጸጥታ አካላት ጥበቃ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ኖንኬባ ሎሲ በበኩላቸው፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት የጥላቻ ጥቃት እና የሕግ ጥሰት በጽኑ እንደሚያወግዝ ገልጸዋል። መንግሥታቸው ጥቃቱን "ከደቡብ አፍሪካ እሴቶች ጋር የሚቃረን" ሲል መግለጹን ያስታወሱት አምባሳደሯ፣ በአሁኑ ወቅት ጥቃቱን በፈጸሙ አካላት ላይ ሰፊ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አምባሳደሯ አክለውም፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንና የምርመራው ውጤት እንደተጠናቀቀ በይፋ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያጋሩ ቃል ገብተዋል። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ሁለቱም ወገኖች የዜጎችን መብት ለማስከበር እና ቀጣናዊ ሰላምን ለማስጠበቅ በዲፕሎማሲያዊ እና በጸጥታ ዘርፎች በቅርበት ለመስራት ተስማምተዋል።

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More
ዜናውን ያጋሩ:

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ